Friday, February 12, 2010

ኦሪት ዘዳግም 34

1፤ ሙሴም ከሞዓብ ሜዳ በኢያሪኮ ፊት ለፊት ወዳለው ወደ ናባው ተራራ ወደ ፈስጋ ራስ ወጣ፤ እግዚአብሔርም እስከዳን ድረስ ያለውን የገለዓድን ምድር፥

2፤ የንፍታሌምንም ምድር ሁሉ፥ የኤፍሬምንና የምናሴንም ምድር፥ እስከ ምዕራብም ባሕር ድረስ ያለውን የይሁዳን ምድር ሁሉ፥ ደቡብንም፥

3፤ እስከ ዞዓር ድረስ ያለውንም የዘንባባ ዛፎች ያሉባትን ከተማ የኢያሪኮን ሸለቆ ሜዳ አሳየው።

4፤ እግዚአብሔርም። ለዘርህ እሰጣታለሁ ብዬ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማልሁላቸው ምድር ይህች ናት፤ በዓይንህ እንድታያት አደረግሁህ፥ ነገር ግን ወደዚያች አትሻገርም አለው።

5፤ የእግዚአብሔር ባሪያም ሙሴ እንደ እግዚአብሔር ቃል በዚያ በሞዓብ ምድር ሞተ።

6፤ በቤተ ፌጎርም ፊት ለፊት በሞዓብ ምድር በሸለቆው ውስጥ ተቀበረ፤ እስከ ዛሬም ድረስ መቃብሩን ማንም አላወቀም።

7፤ ሙሴም በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሀያ ዓመት ነበረ፤ ዓይኑ አልፈዘዘም፥ ጕልበቱም አልደነገዘም።

8፤ የእስራኤልም ልጆች በሞዓብ ሜዳ ሠላሳ ቀን ለሙሴ አለቀሱለት፤ ለሙሴም ያለቀሱለት የልቅሶው ወራት ተፈጸመ።

9፤ ሙሴም እጆቹን ስለ ጫነበት የነዌ ልጅ ኢያሱ የጥበብን መንፈስ ተሞላ፤ የእስራኤልም ልጆች ታዘዙለት፥ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።

10፤ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት እንዳወቀው እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ ከዚያ ወዲህ በእስራኤል ዘንድ አልተነሣም፤

11፤ በግብፅ ምድር በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ ላይ በምድሪቱም ሁሉ ላይ ምልክትንና ድንቅን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ላከው ያለ፥

12፤ በእስራኤል ሁሉ ፊት በጸናች እጅ ሁሉና በታላቅ ማስደንገጥ ሁሉ እንዳደረገው እንደ ሙሴ ያለ አልተነሣም።

ኦሪት ዘዳግም 33

1፤ የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ ሳይሞት የእስራኤልን ልጆች የባረከባት በረከት ይህች ናት።

2፤ እንዲህም አለ።

እግዚአብሔር ከሲና መጣ፥

በሴይርም ተገለጠ፤

ከፋራን ተራራ አበራላቸው፥

ከአእላፋትም ቅዱሳኑ መጣ፤

በስተ ቀኙም የእሳት ሕግ ነበረላቸው።


3፤ ሕዝቡንም ወደዳቸው፤

ቅዱሳኑ ሁሉ በእጅህ ናቸው፤

በእግሮችህም አጠገብ ተቀመጡ፤

ቃሎችህን ይቀበላሉ።


4፤ ሙሴ ለያዕቆብ ጉባኤ ርስት የሆነውን

ሕግ አዘዘን።


5፤ የሕዝቡ አለቆች ከእስራኤል ነገዶች

ሁሉ ጋር በተከማቹ ጊዜ፥

ንጉሥ በይሹሩን ነበረ።


6፤ ሮቤል በህይወት ይኑር፥ አይሙት፤

ሰዎቹም በቍጥር ብዙ ይሁኑ።

7፤ የይሁዳ በረከት ይህ ነው፤ እንዲህም አለ።

አቤቱ፥ የይሁዳን ድምፅ ስማ፥

ወደ ወገኖቹም አግባው፤

እጆቹ ይጠንክሩለት፤

በጠላቶቹ ላይ ረዳት ትሆነዋለህ።

8፤ ስለ ሌዊም እንዲህ አለ፥

ቱሚምህና ኡሪምህ ለቅዱስህ ሰው ነው፥

በማሳህ ለፈተንኸው፥

በመሪባ ውኃም ለተከራከርኸው፤


9፤ ስለ አባቱና ስለ እናቱ። አላየሁም ላለ፥

ወንድሞቹንም ላላስተዋለ፥

ልጆቹንም ላላወቀ፤

ቃልህን አደረጉ፥

ቃል ኪዳንህንም ጠበቁ።


10፤ ፍርድህን ለያዕቆብ፥

ሕግህንም ለእስራኤል ያስተምራሉ፤

በፊትህ ዕጣንን፥

በመሠዊያህም የሚቃጠል መሥዋዕት ይሠዋሉ።


11፤ አቤቱ፥ ሀብቱን ባርክ፥

የእጁንም ሥራ ተቀበል፤

የሚነሣበትን ወገብ ውጋው፥

የሚጠሉትም አይነሡ።

12፤ ስለ ብንያምም እንዲህ አለ።

በእግዚአብሔር የተወደደ በእርሱ

ዘንድ ተማምኖ ይኖራል፤

ቀኑን ሁሉ ይጋርደዋል፥

በትከሻውም መካከል ያድራል።

13፤ ስለ ዮሴፍም እንዲህ አለ፥

ምድሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተባረከ ይሁን፤

በሰማያት ገናንነት በጠል፥

በታችኛውም ቀላይ፥


14፤ በፀሐዩ ፍሬያት ገናንነት፥

በጨረቃውም መውጣት ገናንነት

ኦሪት ዘዳግም 32

ምዕራፍ 32።


1፤ ሰማያት ሆይ፥ አድምጡ፥ እኔም እናገራለሁ፤

ምድርም የአፌን ቃሎች ትስማ።


2፤ ትምህርቴ እንደ ዝናብ ትፈስሳለች፥

ነገሬ እንደ ጠል ትንጠባጠባለች፤

በልምላሜ ላይ እንደ ጤዛ፥

በሣርም ላይ እንደ ካፊያ።


3፤ የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁና፤

ለአምላካችን ታላቅነትን ስጡ።


4፤ እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤

መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፤

የታመነ አምላክ፥ ክፋትም የሌለበት፥

እርሱ እውነተኛና ቅን ነው።


5፤ እነርሱ ረከሱ፤ ልጆቹም አይደሉም፤

ነውርም አለባቸው፤ ጠማማና ገልበጥባጣ ትውልድ ናቸው።


6፤ ደንቆሮ ብልሃተኛም ያልሆንህ ሕዝብ ሆይ፥

ለእግዚአብሔር ይህንን ትመልሳለህ?

የገዛህ አባትህ አይደለምን?

የፈጠረህና ያጸናህ እርሱ ነው።


7፤ የዱሮውን ዘመን አስብ፥

የብዙ ትውልድንም ዓመታት አስተውል፤

አባትህን ጠይቅ፥ ያስታውቅህማል፤

ሽማግሌዎችህን ጠይቅ፥ ይነግሩህማል።


8፤ ልዑል ለአሕዛብ ርስታቸውን ባወረሰ ጊዜ፥

የአዳምን ልጆች በለየ ጊዜ፥

እንደ እስራኤል ልጆች ቍጥር

የአሕዛብን ድንበር አቆመ።


9፤ የእግዚአብሔር እድል ፈንታ ሕዝቡ ነው፤

ያዕቆብም የርስቱ ገምድ ነው።


10፤ በምድረ በዳ በጥማት፥

የነፋስ ጩኸትም በሞላበት ውድማ አገኘው፤

ከበበው ተጠነቀቀለትም፤

እንደ ዓይን ብሌን ጠበቀው።


11፤ ንስር ጫጩቶቹን እንደሚያወጣ፥

በእነርሱም ላይ እንደሚሰፍፍ፥

ክንፎቹን ዘርግቶ ወሰዳቸው፥

በክንፎቹም አዘላቸው።


12፤ እግዚአብሔር ብቻውን መራው፤

ከእርሱም ጋር ሌላ አምላክ አልነበረም።


13፤ በምድር ከፍታ ላይ አወጣው፤

የእርሻውን ፍሬ በላ፤

ከዓለትም ድንጋይ በሚገኝ ማር፥

ከጭንጫውም ድንጋይ በሚገኝ ዘይት አጠባው፤


14፤ የላሙንም ቅቤ፥ የመንጋውም ወተት፥

ከጠቦት ስብ ጋር፥

የባሳንንም አውራ በግ፥ ፍየሉንም፥

ከስንዴ እሸት ጋር በላህ፤

ከወይኑም ደም ያለውን ጠጅ ጠጣህ።


15፤ ይሹሩን ወፈረ፥ ረገጠ፤

ወፈረ፥ ደነደነ፥ ሰባ፤

የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ፤

የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ።


16፤ በሌሎች አማልክት አስቀኑት፥

በርኵሰታቸውም አስቈጡት።


17፤ እግዚአብሔር ላልሆኑ አጋንንት፥

ለማያውቋቸውም አማልክት፥

በቅርብ ጊዜ ለተነሡ ለአዲሶች

አባቶቻቸውም ላልፈሩአቸው አማልክት ሠዉ።


18፤ የወለደህን አምላክ ተውህ፥

ያሳደገህን እግዚአብሔርን ረሳህ።


19፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ስላስቈጡት

እግዚአብሔር አይቶ ጣላቸው።


20፤ እርሱም አለ። ፊቴን እሰውርባቸዋለሁ፤

ፍጻሜያቸው ምን እንደ ሆነ አያለሁ፤

ጠማማ ትውልድ፥

ያልታመኑም ልጆች ናቸው።


21፤ አምላክ ባልሆነው አስቀኑኝ፤

3ቍ.15፤ በዕብራይስጥ ይሹሩን የሚለውን ግዕዙ ያዕቆብ ይለዋል።

በምናምንቴዎቻቸውም አስቈጡኝ፤

እኔም ሕዝብ ባልሆነው አስቀናቸዋለሁ፤

በማያስተውል ሕዝብ አስቈጣቸዋለሁ።


22፤ እሳት ከቍጣዬ ትነድዳለችና፥

እስከ ሲኦል ድረስ ታቃጥላለች፥

ምድርንም ከፍሬዋ ጋር ትበላለች፥

የተራሮችን መሠረት ታነድዳለች።


23፤ መከራን እጨምርባቸዋለሁ፤

በፍላጾቼም እወጋቸዋለሁ።


24፤ በራብ በንዳድ ይጠፋሉ፤

በንዳድና በመራራ ጥፋት ያልቃሉ፤

የአራዊትን ጥርስ፥

የምድርንም እባብ መርዝ እሰድድባቸዋለሁ።


25፤ ጕልማሳውን ከድንግል፥ ሕፃኑንም ከሽማግሌ ጋር፥

በሜዳ ሰይፍ፥ በቤትም ውስጥ ድንጋጤ ያጠፋቸዋል።


26፤ እበትናቸዋለሁ አልሁ፤

ከሰዎችም መካከል መታሰቢያቸውን አጠፋለሁ።


27፤ ነገር ግን ጠላቶቻቸው እንዳይታበዩ።

እጃችን ከፍ ከፍ አለች እንጂ

እግዚአብሔር ይህን ሁሉ አላደረገም

እንዳይሉ፥

ስለ ጠላቱ ቍጣ ፈራሁ።


28፤ ምክር ያጡ ሕዝብ ናቸው፥

ማስተዋልም የላቸውም።


29፤ አእምሮ ቢኖራቸው፥

ይህንን ያስተውሉ ነበር፥

ፍጻሜያቸውንም ያስቡ ነበር።


30፤ እርሱ አምላካቸው ካልሸጣቸው፥

እግዚአብሔርም አሳልፎ ካልሰጣቸው፥

አንድ ሰው እንዴት ሺህን ያሳድድ ነበር?

ሁለቱሳ እንዴት አሥሩን ሺህ ያሸሹ ነበር?


31፤ አምላካችን እንደ አማልክቶቻቸው አይደለም፤

ጠላቶቻችንም ሰነፎች ናቸው።


32፤ ወይናቸው ከሰዶም ወይን፥

ከገሞራም እርሻ ነው፤

ፍሬያቸው ሐሞት ነው፤

ዘለላውም መራራ ነው።


33፤ የወይን ጠጃቸው የእባብ መርዝ፥

የእፉኝትም ሥራይ ነው።


34፤ ይህ በእኔ ዘንድ ተጠብቆ የለምን?

በመዝገቤስ የታተመ አይደለምን?


35፤ የጥፋታቸው ቀን ቀርቦአልና፥

የሚመጣባቸውም ነገር ይፈጥናልና

እግራቸው ሲሰናከል

በቀልና ፍርድ የእኔ ነው።


36፤ ኃይላቸውም እንደ ደከመ፥

የተዘጋ የተለቀቀም እንደሌለ ባየ ጊዜ

እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳል፥

ስለ ባሪያዎቹም ያዝናል።


37፤ እርሱም ይላል። አማልክቶቻቸው የት ናቸው?

ይታመኑባቸው የነበሩት አማልክት?


38፤ የመሥዋዕታቸውን ስብ የበሉ፥

የመጠጥ ቍርባናቸውንም የወይን ጠጅ የጠጡ?

እነርሱ ይነሡ፥ ይርዱአችሁም፥

መጠጊያም ይሁኑላችሁ።


39፤ አሁንም እኔ ብቻዬን እኔ እንደ ሆንሁ፥

ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ እዩ፤

እኔ እገድላለሁ፥ አድንማለሁ፤

እኔ እመታለሁ፥ እፈውስማለሁ፤

ከእጄም የሚያድን የለም።


40፤ እጄን ወደ ሰማይ እዘረጋለሁና፥

እንዲህም እላለሁ። ለዘላለም እኔ ሕያው ነኝና


41፤ የሚንቦገቦግ ሰይፌን እስለዋለሁ፥

እጄም ፍርድን ትይዛለች፥

ጠላቶቼንም እበቀላለሁ፥

ለሚጠሉኝም ፍዳቸውን እከፍላለሁ።


42፤ ከተወጉት ከተማረኩትም ደም፥

ፍላጾቼን በደም አሰክራለሁ፤

ከጠላት አለቆችም ራስ

ሰይፌ ሥጋ ይበላል።


43፤ የባሪያዎቹን ደም ይበቀላልና፥

ጠላቶቹንም ይበቀላቸዋልና፥

ምድሪቱንና ሕዝቡን ይክሳልና

እናንተ አሕዛብ ሆይ፥ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ።

44፤ ሙሴም የነዌም ልጅ ኢያሱ የዚህችን መዝሙር ቃሎች ሁሉ በሕዝቡ ጆሮ ተናገሩ።

45፤ ሙሴም ይህን ቃል ሁሉ ለእስራኤል ሁሉ ተናግሮ ፈጸመ።

46፤ እርሱም እንዲህ አላቸው። የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዝዙበት ዛሬ የምመሰክርላችሁን ቃል ሁሉ በልባችሁ አኑሩት።

47፤ ይህ ነገር ሕይወታችሁ ነው እንጂ ለእናንተ ከንቱ አይደለምና፤ በዚህም ነገር ትወርሱአት ዘንድ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትገቡባት ምድር ረጅም ዘመን ትቀመጣላችሁ።

48፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

49፤ ወደዚህ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ምድር በዓባሪም ተራራ ውስጥ ወዳለው ወደ ናባው ተራራ ውጣ፥ ለእስራኤልም ልጆች ርስት አድርጌ የምሰጣቸውን የከነዓንን ምድር እይ፤

50፤ ወንድምህም አሮን በሖር ተራራ እንደ ሞተ ወደ ወገኖቹም እንደ ተከማቸ፥ በወጣህበት ተራራ ሙት፥ ወደ ወገኖችህም ተከማች፤

51፤ በእስራኤል ልጆች መካከል በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ ባለው በመሪባ ውኃ ስለ በደላችሁኝ፥ በእስራኤልም ልጆች መካከል ስላልቀደሳችሁኝ፥

52፤ ምድሪቱን ፊት ለፊት ታያለህ እንጂ ወደዚያች እኔ ለእስራኤል ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር አትገባም።

ኦሪት ዘዳግም 31

ምዕራፍ 31።

1፤ ሙሴም ሄዶ ይህንን ቃል ለእስራኤል ሁሉ ነገረ።

2፤ አላቸውም። እኔ ዛሬ መቶ ሀያ ዓመት ሆኖኛል፤ ከዚህ በኋላ እወጣና እገባ ዘንድ አልችልም፤ እግዚአብሔርም። ይህን ዮርዳኖስን አትሻገርም ብሎኛል።

3፤ አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ በፊትህ ያልፋል፤ እርሱ እነዚህን አሕዛብ ከፊትህ ያጠፋቸዋል ትወርሳቸውማለህ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ ኢያሱ በፊትህ ይሻገራል።

4፤ እግዚአብሔርም ባጠፋቸው በአሞራውያን ነገሥታት በሴዎንና በዐግ በምድራቸውም እንዳደረገ ያደርግባቸዋል።

5፤ እግዚአብሔርም በፊታችሁ አሳልፎ ይጥላቸዋል፥ እንዳዘዝኋችሁም ትእዛዝ ሁሉ ታደርጉባቸዋላችሁ።

6፤ ጽኑ፥ አይዞአችሁ፥ አትፍሩ፥ ከፊታቸውም አትደንግጡ፤ አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ አይጥልህም፥ አይተውህም።

7፤ ሙሴም ኢያሱን ጠርቶ በእስራኤል ሁሉ ፊት። አንተ ከዚህ ሕዝብ ጋር እግዚአብሔር ለአባቶቻቸው እንዲሰጥ ወደ ማለላቸው ምድር ትገባለህና፥ እርስዋንም ለእነርሱ ታወርሳለህና ጽና፥ አይዞህ።

8፤ በፊትህም የሚሄድ እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ከአንተ ጋር ይሆናል፥ አይጥልህም፥ አይተውህም፤ አትፍራ፥ አትደንግጥ አለው።

9፤ ሙሴም ይህችን ሕግ ጻፈ፥ የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳኑን ታቦት ይሸከሙ ለነበሩት ለሌዊ ልጆች ለካህናቱ ለእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ሰጣት።

10፤ ሙሴም እንዲህ ብሎ አዘዛቸው። በሰባተኛው ዓመት መጨረሻ፥ በዕዳ ምሕረት ዘመን፥ በዳስ በዓል፥

11፤ እስራኤል ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ ዘንድ እርሱ በመረጠው ስፍራ ሲከማች፥ ይህን ሕግ በእስራኤል ሁሉ ፊት በጆሮው አንብበው።

12፤ ይሰሙና ይማሩ ዘንድ፥ አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ይፈሩ ዘንድ፥ የዚህንም ሕግ ቃሎች ሁሉ ጠብቀው ያደርጉ ዘንድ ሕዝቡን ወንዶችንና ሴቶችን ሕፃናቶችንም በአገራችሁ ደጅ ያለውንም መጻተኛ ሰብስብ።

13፤ የሕግ ቃላት የማያውቁ ልጆቻቸውም ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ልትወርሱአት በምትሄዱባት ምድር በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ ይስሙ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርንም መፍራት ይማሩ።

14፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። የምትሞትበት ቀን፥ እነሆ፥ ቀረበ፤ ኢያሱን ጠርተህ እርሱን አዝዘው ዘንድ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከእርሱ ጋር ቁም አለው። ሙሴና ኢያሱም ሄደው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ቆሙ።

15፤ እግዚአብሔርም በድንኳኑ ውስጥ በደመና ዓምድ ተገለጠ፤ የደመናውም ዓምድ በድንኳኑ ደጃፍ ላይ ቆመ።

16፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። እነሆ፥ ከአባቶችህ ጋር ትተኛለህ፤ ይህም ሕዝብ ይነሣል፥ ይቀመጥባትም ዘንድ በሚሄድባት ምድር መካከል ያሉትን ሌሎችን አማልክት ተከትሎ ያመነዝራል፥ እኔንም ይተወኛል፥ ከእነርሱም ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን ያፈርሳሉ።

17፤ በዚያም ቀን ቍጣዬ ይነድድባቸዋል፥ እተዋቸውማለሁ፥ ፊቴንም እሰውርባቸዋለሁ፥ ለአሕዛብ መብል ይሆናሉ፤ በዚያም ቀን። በእውነት እግዚአብሔር በእኛ መካከል የለምና ይህ ክፉ ነገር ሁሉ አገኘን እስኪሉ ድረስ ብዙ ክፉ ነገርና ጭንቀት ይደርስባቸዋል።

18፤ ሌሎችን አማልክት ተከትለዋልና ስላደረጉት ክፋት ሁሉ እኔ በዚያ ቀን ፈጽሜ ፊቴን እሰውራለሁ።

19፤ አሁንም ይህችን መዝሙር ለእናንተ ጻፉ፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተምሩአቸው፤ ይህችም መዝሙር በእስራኤል ላይ ምስክር ትሆንልኝ ዘንድ በአፋቸው አድርጓት።

20፤ ለአባቶቻቸው ወደ ማልሁላቸው፥ ወተትና ማር ወደ ምታፈስሰው ምድር ካገባኋቸው በኋላ፥ ከበሉም ከጠገቡም ከደነደኑም በኋላ፥ ሌሎችን አማልክት ተከትለው ያመልካሉ፥ እኔንም ይንቃሉ፥ ቃል ኪዳኔንም ያፈርሳሉ።

21፤ ዛሬ ወደ ማልሁላቸው ምድር ገና ሳላገባቸው የሚያስቡትን አሳብ አውቃለሁና፥ ከልጆቻቸውም አፍ አትረሳምና ብዙ ክፉ ነገርና ጭንቀት በደረሰባቸው ጊዜ ይህች መዝሙር ምስክር ሆና በፊታቸው ትመሰክራለች።

22፤ ሙሴም በዚያ ቀን ይህችን መዝሙር ጻፈ፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተማራት።

23፤ የነዌንም ልጅ ኢያሱን። የእስራኤልን ልጆች ወደ ማልሁላቸው ምድር ታገባለህና ጽና፥ አይዞህ፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ ብሎ አዘዘው።

24፤ እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ የዚህን ሕግ ቃሎች በመጽሐፍ ከጻፈ ከፈጸመም በኋላ፥

25፤ ሙሴ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት የሚሸከሙትን ሌዋውያንን እንዲህ ብሎ አዘዘ።

26፤ ይህን የሕግ መጽሐፍ ውሰዱ፥ በዚያም በእናንተ ላይ ምስክር እንዲሆን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት አጠገብ አኑሩት።

27፤ እኔ ዓመፃችሁንና የአንገታችሁን ድንዳኔ አውቃለሁና፤ እኔም ዛሬ ከእናንተ ጋር ገና በሕይወት ሳለሁ እናንተ በእግዚአብሔር ላይ ዐምፃችኋል፤ ይልቁንስ ከሞትሁ በኋላ እንዴት ይሆናል?

28፤ ይህን ቃል በጆሮአቸው እናገር ዘንድ፥ ሰማይንና ምድርንም አስመሰክርባቸው ዘንድ የነገዶቻችሁን ሽማግሌዎች ሁሉ አለቆቻችሁንም ሰብስቡልኝ፤

29፤ ከሞትሁ በኋላ ፈጽማችሁ እንድትረክሱ፥ ካዘዝኋችሁም መንገድ ፈቀቅ እንድትሉ አውቃለሁና። በእጃችሁም ሥራ ታስቈጡት ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ስላደረጋችሁ በኋለኛው ዘመን ክፉ ነገር ያገኛችኋል።

30፤ ሙሴም በእስራኤል ጉባኤ ሁሉ ጆሮ የዚህች መዝሙር ቃሎች እስኪፈጸሙ ድረስ ተናገረ።

ኦሪት ዘዳግም 30

ምዕራፍ 30።

1፤ እንዲህም ይሆናል፤ እኔ በፊትህ ያኖርሁት ይህ ነገር ሁሉ፥ በረከቱና መርገሙ፥ በወረደብህ ጊዜ፥ አምላክህም እግዚአብሔር በሚበትንህ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ሆነህ በልብህ ባሰብኸው ጊዜ፥

2፤ ወደ አምላክህም ወደ እግዚአብሔር ተመልሰህ እኔ ዛሬ እንደማዝዝህ ሁሉ አንተና ልጆችህ በፍጹም ልብና በፍጹም ነፍስ ለቃሉ በታዘዝህ ጊዜ፥

3፤ አምላክህ እግዚአብሔር ምርኮህን ይመልሳል ይራራልህማል፤ አምላክህም እግዚአብሔር አንተን ከበተነበት ከአሕዛብ ሁሉ መካከል መልሶ ይሰበስብሃል።

4፤ ሰዎችህም እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ ፈልሰው እንደ ሆነ አምላክህ እግዚአብሔር ከዚያ ይሰበስብሃል፥ ከዚያም ያመጣሃል።

5፤ አባቶችህም ወደ ወረሱአት ምድር አምላክህ እግዚአብሔር ያጋባሃል፥ ትወርሳትማለህ፤ መልካምም ያደርግልሃል፥ ከአባቶችህም ይልቅ ያበዛሃል።

6፤ በሕይወትም እንድትኖር፥ አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ እንድትወድድ አምላክህ እግዚአብሔር ልብህን የዘርህንም ልብ ይገርዛል።

7፤ አምላክህም እግዚአብሔር ይህችን መርገም ሁሉ በጠላቶችህና በሚጠሉህ በሚያሳድዱህም ላይ ያመጣታል።

8፤ አንተም ተመልሰህ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ትሰማለህ፥ ዛሬም እኔ የማዝዝህን ትእዛዙን ሁሉ ታደርጋለህ።

9፤10፤ የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ፥ በዚህም ሕግ መጽሐፍ የተጻፉትን ትእዛዙንና ሥርዓቱን ብትጠብቅ፥ በፍጹምም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ብትመለስ፥ እግዚአብሔር በአባቶችህ ደስ እንዳለው በመልካሙ ነገር ሁሉ እንደ ገና በአንተ ደስ ይለዋልና አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉ በሆድህም ፍሬ በከብትህም ፍሬ በእርሻህም ፍሬ እጅግ ይባርክሃል።

11፤ እኔ ዛሬ የማዝዝህ ይህች ትእዛዝ ከባድ አይደለችም፥ ከአንተም የራቀች አይደለችም።

12፤ ሰምተን እናደርጋት ዘንድ ስለ እኛ ወደ ሰማይ ወጥቶ እርስዋን የሚያመጣልን ማን ነው? እንዳትል በሰማይ አይደለችም።

13፤ ሰምተን እናደርጋት ዘንድ ስለ እኛ ባሕሩን ተሻግሮ እርስዋን የሚያመጣልን ማን ነው? እንዳትል ከባሕሩ ማዶ አይደለችም።

14፤ ነገር ግን ታደርገው ዘንድ ቃሉ በአፍህና በልብህ ውስጥ ለአንተ እጅግ ቅርብ ነው።

15፤ ተመልከት፤ ዛሬ በፊትህ ሕይወትንና መልካምነትን፥ ሞትንና ክፋትን አኑሬአለሁ።

16፤ በሕይወትም እንድትኖር እንድትባዛም፥ አምላክህም እግዚአብሔር ልትወርሳት በምትገባባት ምድር እንዲባርክህ፥ አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድድ ዘንድ፥ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ ትእዛዙንና ሥርዓቱን ፍርዱንም ትጠብቅ ዘንድ ዛሬ እኔ አዝዝሃለሁ።

17፤ ልብህ ግን ቢስት አንተም ባትሰማ፥ ብትታለልም፥ ለሌሎችም አማልክት ብትሰግድ ብታመልካቸውም፥

18፤ ፈጽማችሁ እንድትጠፉ እኔ ዛሬ እነግራችኋለሁ፤ ዮርዳኖስን ተሻግረህ ትወርሳት ዘንድ በምትገባባት ምድር ዘመናችሁን አታስረዝሙም።

19፤ በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ፤ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ፤

20፤ እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እንዲሰጣቸው በማለላቸው በምድሪቱ ትቀመጥ ዘንድ፥ እርሱ ሕይወትህ የዘመንህም ርዝመት ነውና አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድደው ትጠባበቀውም ቃሉንም ትሰማ ዘንድ ምረጥ።

ኦሪት ዘዳግም 29

ምዕራፍ 29።

1፤ እግዚአብሔር በኮሬብ ካደረገው ቃል ኪዳን ሌላ በሞዓብ ምድር ከእስራኤል ልጆች ጋር ያደርገው ዘንድ ሙሴን ያዘዘው የቃል ኪዳኑ ቃሎች እነዚህ ናቸው።

2፤ ሙሴም የእስራኤልን ልጆች ሁሉ ጠርቶ አላቸው። እግዚአብሔር በፊታችሁ በግብፅ ምድር በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ በምድሩም ሁሉ ያደረገውን ሁሉ፥

3፤ ዓይኖቻችሁ ያዩአቸውን ታላላቆች ፈተናዎች፥ ታላላቆች ተአምራትና ድንቆች፥ አይታችኋል፤

4፤ እግዚአብሔር ግን አስተዋይ ልብ፥ የሚያዩ ዓይኖች፥ የሚሰሙም ጆሮች እስከ ዛሬ ድረስ አልሰጣችሁም።

5፤ አርባ ዓመት በምድረ በዳ መራኋችሁ፤ ልብሳችሁም አላረጀባችሁም፥ ጫማችሁም በእግራችሁ ላይ አላረጀም።

6፤ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ እንጀራ አልበላችሁም፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክረውን መጠጥ አልጠጣችሁም።

7፤ ወደዚህም ስፍራ በመጣችሁ ጊዜ የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎን የባሳንም ንጉስ ዐግ ሊወጉን ወጡብን፥ እኛም መታናቸው፤

8፤ ምድራቸውንም ወስደን ለሮቤልና ለጋድ ለምናሴም ነገድ እኵሌታ ርስት አድርገን ሰጠናቸው።

9፤ ስለዚህ በምታደርጉት ሁሉ ትከናወኑ ዘንድ የዚህን ቃል ኪዳን ቃሎች ጠብቁ አድርጉም።

10፤11፤ ሁላችሁ፥ አለቆቻችሁም ነገዶቻችሁም ሽማግሌዎቻችሁም ሹማምቶቻችሁም፥ የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ልጆቻችሁም ሴቶቻችሁም በሰፈራችሁም ያለ እንጨትህን የሚቈርጥ ውኃህንም የሚቀዳ መጻተኛ፥ ዛሬ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ቆማችኋል፤

12፤13፤ ይኸውም ዛሬ ለእርሱ ሕዝብ አድርጎ ያስነሣህ ዘንድ፥ እርሱም ለአንተ እንደ ተናገረ ለአባቶችህም ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እንደ ማለ አምላክ ይሆንልህ ዘንድ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ዛሬ በሚያደርገው ቃል ኪዳን ትገባ ዘንድና የአምላክህን የእግዚአብሔርን መሐላ ትሰማ ዘንድ ነው።

14፤ እኔም ይህን ቃል ኪዳንና ይህን መሐላ የማደርገው ከእናንተ ጋር ብቻ አይደለም፤

15፤ ነገር ግን ዛሬ በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ከእኛ ጋር በዚህ ከሚቆም ሰው ጋር፥ ዛሬም ከእኛ ጋር በዚህ ከሌለ ሰው ጋር ነው እንጂ፤

16፤ ነገር ግን እኛ በግብፅ ምድር እንደ ተቀመጥን በመካከላቸውም ባለፋችሁባቸው አሕዛብ መካከል እንዳለፍን አውቃችኋልና፥

17፤ ርኩስነታቸውንም በእነርሱም ዘንድ የነበሩትን የእንጨትና የድንጋይ የብርና የወርቅም ጣዖቶቻቸውን አይታችኋልና፥

18፤ ሄዶ የእነዚያን አሕዛብ አማልክት ያመልክ ዘንድ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ልቡን ዛሬ የሚያስት ወንድ ወይም ሴት ወይም ወገን ወይም ነገድ አይኑርባችሁ፤ ሐሞትና እሬትም የሚያበቅል ሥር አይሁንባችሁ።

19፤ የዚህንም እርግማን ቃሎች የሰማ ሰው። ምንም እንኳ በልቤ ደንዳንነት ብሄድ፥ ለጥማቴም ስካር ብጨምር፥ ሰላም ይሆንልኛል ብሎ ሰውነቱን በልቡ የሚባርክ ቢኖር፥

20፤ የእግዚአብሔር ቍጣ ቅንዓቱም በዚያ ሰው ላይ ይጤሳል እንጂ እግዚአብሔር ይቅርታ አያደርግለትም፤ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈው እርግማን ሁሉ በላዩ ይኖራል፥ እግዚአብሔርም ስሙን ከሰማይ በታች ይደመስሰዋል።

21፤ እግዚአብሔርም በዚህ ሕግ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው እንደ ቃል ኪዳኑ እርግማን ሁሉ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ለጥፋት ይለየዋል።

22፤ ከዚያም በኋላ የሚነሣ ትውልድ ከእናንተም በኋላ የሚሆኑ ልጆቻችሁ ከሩቅ አገርም የሚመጣ እንግዳ፥ የዚህን አገር መቅሠፍት፥ እግዚአብሔርም በእርስዋ ያደረገውን ሥቃይዋን፥

23፤ ምድርም በሁለንተናዋ ዲንና ጨው መቃጠልም እንደ ሆነባት፥ እንዳትዘራም እንዳታበቅልም፥ ማናቸውም ሣርና ልምላሜም እንዳይወጣባት፥ እግዚአብሔር በቍጣውና በመዓቱ እንደ ገለባበጣቸው እንደ ሰዶምና ገሞራ እንደ አዳማና እንደ ሲባዮ እንደ ሆነች ባዩ ጊዜ፥

24፤ አሕዛብ ሁሉ። እግዚአብሔር በዚህች ምድር ስለ ምን እንደዚህ አደረገ? ይህስ የቍጣው ታላቅ መቅሠፍት ምንድር ነው? ይላሉ።

25፤ ሰዎችም እንዲህ ይላሉ። የአባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን ስለተዉ፥

26፤ ሄደውም የማያውቋቸውንና ያልታዘዙትን ሌሎችን አማልክት ስላመለኩና ስለ ሰገዱላቸው፥

27፤ ስለዚህ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን መርገም ሁሉ ያወርድባት ዘንድ የእግዚአብሔር ቍጣ በዚህች ምድር ነደደ፤

28፤ ዛሬም እንዳሉ እግዚአብሔር በቍጣና በመቅሠፍት በታላቅም መዓት ከምድራቸው ነቀላቸው፥ ወደ ሌላም ምድር ጣላቸው።

29፤ ምሥጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ እናደርግ ዘንድ ለእኛ ለዘላለምም ለልጆቻችን ነው።

ኦሪት ዘዳግም 28

1፤ እንዲህም ይሆናል፤ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ትእዛዙን ሁሉ ብታደርግ ብትጠብቅም አምላክህ እግዚአብሔር ከምድር አሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያደርግሃል።

2፤ የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ይመጡልሃል፤ ያገኙህማል።

3፤ አንተ በከተማ ቡሩክ ትሆናለህ፥ በእርሻም ቡሩክ ትሆናለህ።

4፤ የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የከብትህም ፍሬ፥ የላምህም ርቢ፥ የበግህም ርቢ ቡሩክ ይሆናል።

5፤ እንቅብህና ቡሃቃህ ቡሩክ ይሆናል።

6፤ አንተም በመግባትህ ቡሩክ ትሆናለህ፥ በመውጣትህም ቡሩክ ትሆናለህ።

7፤ እግዚአብሔርም በላይህ የሚቆሙትን ጠላቶችህን በፊትህ የተመቱ ያደርጋቸዋል፤ በአንድ መንገድ ይመጡብሃል፥ በሰባትም መንገድ ከፊትህ ይሸሻሉ።

8፤ እግዚአብሔር በረከቱ በአንተ ላይ በጐተራህ በእጅህም ሥራ ሁሉ እንዲወርድ ያዝዛል፤ አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህም ምድር ይባርክሃል።

9፤ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትጠብቅ፥ በመንገዱም ብትሄድ፥ እግዚአብሔር እንደ ማለልህ ለእርሱ የተቀደሰ ሕዝብ አድርጎ ያቆምሃል።

10፤ የምድር አሕዛብም ሁሉ የእግዚአብሔር ስም በአንተ ላይ እንደ ተጠራ አይተው ይፈሩሃል።

11፤ እግዚአብሔርም እርስዋን ይሰጥህ ዘንድ ለአባቶችህ በማለላቸው በምድርህ ላይ፥ በሆድህ ፍሬ፥ በከብትህ ፍሬ፥ በእርሻህም ፍሬ፥ እግዚአብሔር በጎነቱን በላይህ ያበዛል።

12፤ እግዚአብሔርም ለምድርህ በወራቱ ዝናብ ይሰጥ ዘንድ፥ የእጅህንም ሥራ ሁሉ ይባርክ ዘንድ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል፤ ለብዙ አሕዝብም ታበድራለህ፥ አንተ ግን ከማንም አትበደርም።

13፤14፤ ዛሬም ያዘዝሁህን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሰምተህ ብትጠብቃት ብታደርጋትም፥ ዛሬም ካዘዝሁህ ከእነዚህ ቃሎች ወደ ቀኝ ወደ ግራም ፈቀቅ ባትል፥ ታመልካቸውም ዘንድ ሌሎችን አማልክት ባትከተል፥ እግዚአብሔር ራስ ያደርግሃል እንጂ ጅራት አያደርግህም፤ ሁልጊዜም በላይ እንጂ በታች አትሆንም።

15፤ ነገር ግን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ ባትጠብቅ ባታደርግም፥ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል ያገኙህማል።

16፤ በከተማ ርጉም ትሆናለህ፥ በእርሻም ርጉም ትሆናለህ።

17፤ እንቅብህና ቡሃቃህ ርጉም ይሆናል።

18፤ የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የላምህም ርቢ፥ የበግህም ርቢ ርጉም ይሆናል።

19፤ አንተ በመግባትህ ርጉም ትሆናለህ፥ በመውጣትህም ርጉም ትሆናለህ።

20፤ እኔን ስለ ተውኸኝ፥ ስለ ሥራህ ክፋት፥ እስክትጠፋ ፈጥነህም እስክታልቅ ድረስ በምትሠራው ሥራ ሁሉ እግዚአብሔር መርገምን፥ ሽሽትን፥ ተግሣጽን ይሰድድብሃል።

21፤ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ ከምትገባባት ምድር እስኪያጠፋህ ድረስ ቸነፈርን ያጣብቅብሃል።

22፤ እግዚአብሔር በክሳት፥ በንዳድም፥ በጥብሳትም፥ በትኲሳትም፥ በድርቅም፥ በዋግም፥ በአረማሞም ይመታሃል፤ እስክትጠፋም ድረስ ያሳድዱሃል።

23፤ በራስህም ላይ ሰማይ ናስ ይሆንብሃል፥ ከእግርህም በታች ምድሪቱ ብረት ትሆንብሃለች።

24፤ እግዚአብሔር የምድርህን ዝናብ ትቢያና አፈር ያደርጋል፤ እስክትጠፋ ድረስ ከሰማይ ይወርድብሃል።

25፤ እግዚአብሔር ከጠላቶችህ ፊት የተመታህ ያደርግሃል፤ በአንድ መንገድ ትወጣባቸዋለህ፥ በሰባት መንገድ ከእነርሱ ትሸሻለህ፤ ለምድርም መንግሥታት ሁሉ ድንጋጤ ትሆናለህ።

26፤ ሬሳህ ለሰማይ ወፎች ሁሉ ለምድርም አራዊት መብል ይሆናል፥ የሚያስፈራቸውም የለም።

27፤ እግዚአብሔር ፈውስ በሌለው በግብፅ ቍስል በእባጭም በቋቁቻም በችፌም ይመታሃል።

28፤ እግዚአብሔር በዕብደት፥ በዕውርነት፥ በድንጋጤም ይመታሃል።

29፤ በቀትርም ጊዜ ዕውር በጨለማ እንደሚርመሰመስ ትርመሰመሳለህ፥ መንገድህም የቀና አይሆንም፤ በዘመንህም ሁሉ የተጨነቅህ የተዘረፍህም ትሆናለህ፥ የሚያድንህም የለም።

30፤ ሚስት ታጫለህ፥ ሌላም ሰው ከእርስዋ ጋር ይተኛል፤ ቤት ትሠራለህ፥ አትቀመጥበትም፤ ወይን ትተክላለህ፥ ከእርሱም አትበላም።

31፤ በሬህ በፊትህ ይታረዳል፥ ከእርሱም አትበላም፤ አህያህ ከእጅህ በግድ ይወሰዳል፥ ወደ አንተም አይመለስም፤ በግህ ለጠላቶችህ ትሰጣለች፥ የሚያድንህም አታገኝም።

32፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ለሌላ ሕዝብ ይሰጣሉ፥ ዓይኖችህም ያያሉ፥ ሁልጊዜም ስለ እነርሱ ሲባክኑ ያልቃሉ፤ በእጅህም ኃይል ምንም አይገኝም።

33፤ የምድርህን ፍሬ ድካምህንም ሁሉ የማታውቀው ሕዝብ ይበላዋል፤ አንተም ሁልጊዜ የተጨነቅህ የተገፋህም ትሆናለህ።

34፤ ዓይኖችህም ከሚያዩት የተነሣ ዕብድ ትሆናለህ።

35፤ እግዚአብሔር ፈውስ በሌለው በክፉ ቍስል ጕልበትህንና ጭንህን ከእግርህ ጫማ እስከ አናትህ ድረስ ይመታሃል።

36፤ እግዚአብሔርም አንተን በአንተም ላይ የምታነግሠውን ንጉሥ አንተና አባቶችህ ወዳላወቃችኋቸው ሕዝብ ይወስድሃል፤ በዚያም ሌሎችን የእንጨትና የድንጋይ አማልክት ታመልካለህ።

37፤ እግዚአብሔርም በሚያገባህ በአሕዛብ መካከል ሁሉ ድንጋጤ ምሳሌም ተረትም ትሆናለህ።

38፤ እጅግ ዘር ወደ እርሻ ታወጣለህ፤ አንበጣም ይበላዋልና ጥቂት ትሰበስባለህ።

39፤ ወይን ትተክላለህ ታበጀውማለህ፤ ትልም ይበላዋልና ከእርሱ ምንም አትሰበስብም፥ የወይን ጠጁንም አትጠጣም።

40፤ የወይራ ዛፍ በአገርህ ሁሉ ይሆንልሃል፤ ወይራህም ይረግፋልና ዘይቱን አትቀባም።

41፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይወለዱልሃል፤ በምርኮም ይሄዳሉና ለአንተ አይሆኑልህም።

42፤ ዛፍህን ሁሉ የምድርህንም ፍሬ ኩብኩባ ይወርሰዋል።

43፤ በአንተ መካከል ያለ መጻተኛ በአንተ ላይ ከፍ ከፍ ይላል፥ አንተም ዝቅ ዝቅ ትላለህ።

44፤ እርሱ ያበድርሃል፥ አንተ ግን አታበድረውም፤ እርሱ ራስ ይሆናል፥ አንተም ጅራት ትሆናለህ።

45፤ የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ስላልሰማህ፥ ያዘዘህንም ትእዛዙንና ሥርዓቱን ስላልጠበቅህ፥ እስክትጠፋ ድረስ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይወርዱብሃል፥ ያሳድዱህማል፥ ያገኙሁማል።

46፤ በአንተም በልጅ ልጅህም ላይ ለዘላለም ለምልክትና ለድንቅ ይሆናሉ።

47፤ ሁሉን አብዝቶ ስለ ሰጠህ አምላክህን እግዚአብሔርን በፍሥሐና በሐሤት አላመለክህምና

48፤ በራብና በጥማት በዕራቁትነትም ሁሉንም በማጣት እግዚአብሔር ለሚልክብህ ለጠላቶችህ ትገዛለህ፤ እስኪያጠፋህም ድረስ በአንገትህ ላይ የብረት ቀንበር ይጭናል።

49፤50፤ እግዚአብሔር ቋንቋቸውን የማታውቀውን፥ ፊታቸው የደነደነውን፥ ሽማግሌውንም የማያፍሩትን፥ ሕፃኑንም የማይምሩትን ሕዝብ ንስር እንደሚበርር ከሩቅ አገር ከምድር ዳር ያመጣብሃል።

51፤ እስክትጠፋ ድረስ የከብትህን ፍሬ የምድርህንም ፍሬ ይበላሉ፤ እስኪያጠፉህም ድረስ እህልን የወይንም ጠጅ ዘይትንም የላምህንና የበግህን ርቢ አይተዉልህም።

52፤ በአገርህ ሁሉ ያሉ፥ ትታመንባቸው የነበሩ፥ የረዘሙ የጸኑም ቅጥሮች እስኪፈርሱ ድረስ፥ በከተሞችህ ደጆች ሁሉ ከብበው ያስጭንቁሃል፤ አምላክህም እግዚአብሔር በሰጠህ ምድር ሁሉ በደጆች ሁሉ ከብበው ያስጨንቁሃል።

53፤ ጠላቶችህም ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ አምላክህ እግዚአብሔር የሚሰጥህን የሆድህን ፍሬ የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ሥጋ ትበላለህ።

54፤ በአንተ ዘንድ የተለሳለሰና በቅምጥልነት ሁልጊዜ ይኖር የነበረ ሰው በወንድሙ፥ አቅፋውም በምትተኛ በሚስቱ፥ በቀሩትም ልጆች ይቀናል፤

55፤ በደጆችህ ሁሉ ውስጥ ጠላቶችህ ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ ሌላ ነገር የቀረው የለምና ከሚበላው ከልጆቹ ሥጋ ለአንዱ አይሰጥም።

56፤ በአንተ ዘንድ ያለችው የተለሳለሰችና በቅምጥልነት ሁልጊዜ ትኖር የነበረችው፥ ከልስላሴና ከቅምጥልነት የተነሣ የእግር ጫማዋን በምድር ላይ ያላደረገችው ሴት፥ አቅፋ በተኛችው ባልዋ፥

57፤ በወንድና በሴት ልጅዋም፥ በእግርዋ መካከል በሚወጣው በእንግዴ ልጅ፥ በምትወልዳቸውም ልጆች ትቀናለች፤ በደጆችህም ውስጥ ጠላቶችህ ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ ሁሉን ስላጣች በስውር ትበላቸዋለች።

58፤ በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ታደርግ ዘንድ ባትጠብቅ፥ ይህንንም <<አምላክህ እግዚአብሔር>> የተባለውን የተመሰገነውንና የተፈራውን ስም ባትፈራ፥

59፤ እግዚአብሔር መቅሠፍትህን፥ የዘርህንም መቅሠፍት፥ ብዙ ዘመንም የሚኖረውን ታላቅ መቅሠፍት፥ ብዙ ዘመን የሚኖረውንም ክፉ ደዌ ያደርግብሃል።

60፤ የፈራኸውንም የግብፅ ደዌ ሁሉ እንደ ገና ያመጣብሃል፥ ይጣበቅብህማል።

61፤ ደግሞም ይህ ሕግ ባለበት መጽሐፍ ውስጥ ያልተጻፈውን ደዌ ሁሉ መቅሠፍትም ሁሉ እስክትጠፋ ድረስ እግዚአብሔር ያመጣብሃል።

62፤ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማችሁምና ከብዛታችሁ የተነሣ እንደ ሰማይ ከዋክብት የነበረው ቍጥራችሁ ጥቂት ሆኖ ይቀራል።

63፤ እግዚአብሔርም በጎ ያደርግላችሁ ዘንድ ያበዛችሁም ዘንድ ደስ ይለው እንደ ነበረ፥ እንዲሁ እግዚአብሔር ሲያጠፋችሁ ሲያፈርሳችሁም ደስ ይለዋል፤ ትወርሱአትም ዘንድ ከምትገቡባት ምድር ትነቀላላችሁ።

64፤ እግዚአብሔርም ከምድር ዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ ወዳሉ አሕዛብ ሁሉ ይበትንሃል፤ በዚያም አንተና አባቶችህ ያላወቃችኋቸውን ሌሎችን አማልክት፥ እንጨትንና ድንጋይን፥ ታመልካለህ።

65፤ በእነዚያም አሕዛብ መካከል ዕረፍት አታገኝም፥ ለእግርህም ጫማ ማረፊያ አይሆንም፤ በዚያም እግዚአብሔር ተንቀጥቃጭ ልብ፥ ፈዛዛ ዓይን፥ ደካማም ነፍስ ያመጣብሃል።

66፤ ነፍስህም ታመነታለች፤ ሌሊትና ቀንም ትፈራለህ፥ በሕይወትህም አትታመንም፤

67፤ አንተ ስለ ፈራህበት ስለ ልብህ ፍርሃት፥ በዓይንህም ስለምታየው አስተያየት፥ ማለዳ። መቼ ይመሻል? ትላለህ፤ ማታም። መቼ ይነጋል? ትላለህ።

68፤ ከእንግዲህ ወዲህ ተመልሰህ አታያትም ባልሁህ መንገድም እግዚአብሔር በመርከብ ወደ ግብፅ ይመልስሃል፤ በዚያም ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎች ትሆኑአቸው ዘንድ ለጠላቶቻችሁ ራሳችሁን ትሸጣላችሁ፤ የሚገዛችሁም አይገኝም።